08/05/2026
ከባህላዊ ድካም ወደ ዘመናዊ ስኬት፦ የፋስት ጠጠር ማምረቻ የድል ጉዞ
“በልማት ባንክ ህልማችን እውን ሆኗል!” — አቶ አብዲኑር ሙክታር፣ የፋስት ጠጠር ማምረቻ ባለቤት
በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጂግጂጋ ዲስትሪክት ውስጥ የሚገኘው “ፋስት የጠጠር ማምረቻ” ዛሬ ላይ የክልሉን የኮንስትራክሽን ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየመለሰ የሚገኝ ስኬታማ ፕሮጀክት ነው። ነገር ግን ከዚህ ስኬት በስተጀርባ በአቶ አብዲኑር ሙክታር የሚመራ ትልቅ ጥረት እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ ድጋፍ ውጤት የሆነ ተስፋ ሰጪ ታሪክ አለ።
ለውጥ ያመጣው መረጃ
ቀደም ሲል ፋስት ጠጠር ማምረቻ ስራውን የሚያከናውነው በእጅ በሚሰሩ ባህላዊ የድንጋይ ወፍጮዎች ነበር። ስራው እጅግ አድካሚ ከመሆኑም ባለፈ ምርታማነቱ በቀን ከአንድ ወይም ሁለት መኪና አይዘልም ነበር። ይህንን አድካሚ ሂደት የተመለከቱ የልማት ባንክ ባለሙያዎች ለባለቤቱ ለአቶ አብዲኑር በባንኩ በኩል ዘመናዊ ማሽን በሊዝ ፋይናንሲንግ ማግኘት እንደሚችሉ መረጃ ሰጧቸው።
አቶ አብዲኑርም ያገኙትን መረጃ በመጠቀምና የባንኩን መስፈርት በማሟላት በ90 ሚሊዮን ብር ካፒታል ዘመናዊ የጠጠር ማምረቻ ማሽን (ክሬሸር) ባለቤት ለመሆን በቁ።
ከ2 ወደ 30፦ የተመዘገበ አስደናቂ ስኬት
ዘመናዊው ማሽን ከቻይና መጥቶ በባለሙያዎች ከተገጣጠመ በኋላ በፋብሪካው ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። በቀን 1 እና 2 መኪና ብቻ ያመርት የነበረው ድርጅት፣ ዛሬ በቀን ከ20 እስከ 30 መኪና ጠጠር ማምረት ችሏል።
"ይህ እጅግ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ልማት ባንክን በጣም እናመሰግናለን" ይላሉ አቶ አብዲኑር።
የስራ እድል ፈጠራ እና የገበያ ትስስር
በአሁኑ ሰዓት በጂግጂጋ ከተማ በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ በመሆኑ የድርጅቱ ምርት ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የጥሬ እቃ አቅርቦትም ሆነ የገበያ ትስስር ችግር ስለሌለበት ጠጠር ማምረቻ ማሽናቸው /ክሬሽር/ በጅጅጋ ከተማ ከሚገኙ ጥቂቶች አንዱ መሆኑንና ምርታችውም በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከ20 በላይ ወጣቶች በአንድ ፈረቃ ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል። በቅርቡ ስራውን በሁለት ፈረቃ በማሳደግ ለተጨማሪ 20 ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ዝግጅቱን አጠናቋል።
ተስፋ ካለመቁረጥ እስከ ሁለንተናዊ ስኬት
ጉዞው ሁሌም አልጋ በአልጋ አልነበረም። አቶ አብዲኑር እንደገለጹት፣ ከመንገድ፣ ከመብራት እና ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ስራውን እስከመተው ያደረሱ ተግዳሮቶች አጋጥመዋቸው ነበር። ነገር ግን የልማት ባንክ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ ተስፋ እንዲሰንቁ እና ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።
ዛሬ ላይ ፋስት ጠጠር ማምረቻ በጠጠር ብቻ አልተወሰነም። ከባንኩ ጋር በመተባበር የብሎኬት ማምረቻ፣ የአርማታ (Ready-mix Concrete) ስራ እና የውሃ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ ጀምሯል።
መልዕክት ለሌሎች ወጣቶች
አቶ አብዲኑር ሙክታር በክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች እና ስራ ፈጣሪዎች የሚከተለውን ምክር ያስተላልፋሉ፦ "ወጣቶች ከእኛ ተሞክሮ በመነሳት፣ አዳዲስም ሆነ የጀመሯቸው ፕሮጀክቶች ካሉ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር እንዲሰሩ እመክራለሁ። የባንኩ ባለሙያዎች አቀባበል እና ድጋፍ ስራን አዋጭ ያደርጋል፤ ያሰቡትንም ለማሳካት ትልቅ አጋር ነው!"