18/03/2026
አዋሽ ባንክ ሦስት የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን አስጀመረ
:
አቢሲኒያ ባንክና ቪዛ ካርድ ድንበር ተሻጋሪ ክፍያን ለማስፋፋት ተስማሙ
አዋሽ ባንክ በስድስት ወሮች ብቻ በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀስ መቻሉንና ለሬሚታንስ የገንዘብ ዝውውር መተግበሪያ የሚሆን ፕላትፎርም ጨምሮ ሦስት የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ማስገባቱን አስታወቀ፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ከቪዛ ካርድ ጋር ስትራቴጂክ ያለው ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
አዋሽ ባንክ ባለፈው ሐሙስ ሦስቱን አዲስ የዲጂታል አገልግሎት ባስተዋወቀበት ፕሮግራም ላይ እንደገለጸው በደጂታል የባንክ አገልግሎት ዘርፍ እየታየ ያለው የገንዘብ እንቅስቃሴ በእጅጉ እየጨመረ ነው፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት ባንኩ ባሉት የተለያዩ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች እየሰጠ ያለው አገልግሎት በእጅጉ እየጨመረ በመምጣቱ ከሐምሌ 2017 እስከ ታኅሳስ 2018 ዓ.ም. ባሉት በስድስት ወራት ብቻ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡
ይህን ያህል መጠን ያለው እንቅስቃሴ ያደረገው ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ያደረጋቸው የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ከግለሰቦች አልፎ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማካተት የተለያዩ አገልግሎቶችን በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡
በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት አገልግሎት እየሰጠባቸው ካሉት መካከል የኤሌክትሪክና የውኃ ክፍያ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ዲጂታል የብድር አገልግሎቶችና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡