24/09/2018
ሰቆቃው ጴጥሮስ
• • •
ከጴጥሮስ– ያቺን ሰዓት ቴአትር
✍✍✍✍✍
አዬ፥ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፥ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፥ ሰቀቀንዋን፥ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን፥ በፋሽታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፥ ተምሳ፥ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፥ እንደኰረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፥ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፥ ብኩን፥ መፃጉዕ ናት፤…
እና ፈርቼ እንዳልባክን፥ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፥ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፥ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን።
አዎን፥ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ፥
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፥ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ…
አዋጅ፥ የምሥራች ብዬ፥ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከናቴ ማኅፀን አልፌ
በኢትዮጵያ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃን እግሬ ድሄባት፥ በሕልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፥ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩትና ከጥጃ፥ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፥ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
የገጠር የደመና ዳስ፥ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅና ከሚዳቋ፥ ከዥግራ ጠረን ስተሻሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፥ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስንገጥም፥ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፥ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ
ለጥማድ በሬዎች ራት፥ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ፥
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሣው ሥር ጐጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፥ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፥ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፥ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፥ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፥ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፥በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ....
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያቺን የልጅነት ምስራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፥ የምኞትየተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፥ጥርሶችሽን ትነክሽባት?
•••
ስሜን በስምሽ ሰይሜ፥ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፥ከድጓ ቤት እመጻሕፍት፥
ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፥ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀሰላም፥ከቤተልሔም ቅዳሴ
አኰ፥ቀፎ ፥ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግሥ ገሦ
መቅደስ አጥኖ፥ ማኅሌት ቆሞ
በልብስ ተክህኖ አጊጦ፥ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሃን ያንቺ ጽላት፥ነፍሴ ላይ በሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ፥ረድ ሆኜ አብሮኝ ታድሞ
ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፥ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ፤
ስሜን በስምሽ ሰይሜ፥ ሆነሽኝ የእምነቴ ፋኖስ
በዋዜማሽ ግሸን ማርያም፥ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፥በወንበሩ አኖርሺኝ፥ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ፤
ታዲያን ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፥ ከምትሰጪኝ ለፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት ዕድሜ፥ ዓይኔን በጓጐጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፥ ወርዶ በጭለማ በርኖስ።
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፥ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፥ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፤
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፥ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፥ገላዋ ገላዬ እንዲሆን።…
አዎን ፥ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እፀናበት ልብ አጣሁ።…
••••
ሕፃን ሆኜ የእርግብ ጫጩት፥አንዳንዴ ራብ ሲያዳክማት
ችጋር ከጐጆዋ ገፍቶ፥ እዛፍ ግርጌ ሲጥላት
እናቷ በርራ ደርሳላት
በአክናፏ ሙቀት ታቅፋት
እፍ እያለች ግንባሯ ላይ፥ሕይወት ስትነፍስባት
ወዲያው ነፍስ ትዘራለች
ሽር -ብር-ትር እያለች።
ባክሽ አንቺም አትራቂብኝ
እመ ብርሃን እናቴ፥ትንፋሽሽን እፍ በዪብኝ
ፅናትሽን እፍ በዪብኝ፥
ወይም ይቺን የሞት ጽዋ፥ ጥላዋ ነፍሴን ካፈናት
እንዳልጠጣት አሳልፊያት
መራራ ክንፏን ገንጥለሽ፥ቀጠሮ፥ ቃልዋን ግደፊያት፤....
አለዚያም ጽናትሽን ስጪኝ፥ልጠጣው ኪዳነ-ውሉን
የኔ ፈቃድ እምነትሽ ነው፥ያንቺ ፈቃድ ብቻ ይሁን።
እንደ ጳውሎስ እንድጸና፥ በፍርሃት እንዳልታሰር
በውስጤ ከሚታገለኝ፥ በሥጋ አውሬ እንዳልታወር
ለየዕለቱ ሞት እንዳልሰንፍ
የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥፍ
ቃልሽ በሕሊናዬ ዲብ ፥ ኃይልሽ በሕዋሴ ይረፍ።
ፍርሃት ቢያረብብኝም፥ አንቺ ካለሺኝ አልሰጋም
ኩርምት ብዬ እችልበት፥ እሸሸግበት አይጠፋም
የግማደ መስቀሌን ጉጥ፥ እታገስበት አላጣም፥
አለዚያማ ብቻዬን ነኝ፥ ኢትዮጵያም አላንቺ የላት
አንቺ አፅኝኝ እንድጸናላት።
አስርጪብኝ የእምነት ቀንጃ፥ ለሥጋቴ አጣማጅ አቻ
ለጭንቀቴ– መቀነቻ።..。
አዎን፥ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ…
✍✍✍✍✍
እሳት ወይ አበባ
(ከሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን)